ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ታህሳስ 19 እና 20/2016 የምክክር መድረክ አካሄደ።
በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር በተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የተመራዉና በኮሚሽኑ የ2016 በጀት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ፣ ተቋማዊ ፕሮግራም እና ፕሮጀክቶች እንዲሁም የቀድሞ ተዋጊዎች የምዝገባ ስርዓት እና የአመዘጋገብ ሂደቶች ላይ ያተኮረዉ የሁለት ቀናት ምክክር በተሳካ መልኩ ተካሂዶ ተጠናቋል።
በምክክሩ ተቋሙ አዲስ ከመሆኑ አኳያ በመጀመሪያዉ ግማሽ ዓመት ዋነኛ ትኩረቱ ተቋሙን በተሟላ መልኩ ማደራጀትና ለተልዕኮዉ ዝግጁ ወደሆነ ቁመና ማድረስ ሲሆን አፈፃፀሙም በአብዛኛው የተሳካ መሆኑ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
በሌላ በኩልም በውይይቱ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት እንዲያስችል የተዘጋጀዉ ረቂቅ የዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ማዕቀፍና ይህንኑ ፕሮግራም መነሻ ያደረጉ ሶስት ፕሮጀክቶች ቀርበዉ ምክክር ተደርጎባቸዋል። ሰነዶች ከባለድርሻ አካላት በተደረጉ ተከታታይ ምክክሮች የዳበሩና በቀጣይ ሀብት ለማሰባሰብ በሚያስችል ደረጃ መዘጋጀታቸው በዉይይቱ ተወስቶ ሰነዱን የበለጠ ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶች ተሰጥተዋል።
በመጨረሻም የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ምዘገባ ለማካሄድና መረጃዉን ለማስተዳደር የሚያስችል አሰራር ቀርቦ ዉይይት ተደርጓል ።
በዚሁ የሁለት ቀናት የዉይይት መድረክ ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመራሮችና ሰራተኞች በተጨማሪ ከፌዴራል ተቋማት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ሀላፊ ፣ የጤና፣ የስራና ክህሎት፣ የገንዘብ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እና የትምህርት ሚኒሰቴር ተወካዮች እንዲሁም የኮሚሽኑ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ አመራሮች ተገኝተዋል።