የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሠራተኞች የሰንደቅ ዓላማን ቀን በድምቀት አከበሩ!
በየዓመቱ ጥቅምት 5 ቀን የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለ16ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ተከብሮ ውሏል። የአንድ አገር መለያ ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያችን የአባቶቻችንና የእናቶቻችን የነጻነትና የመስዋዕትነት ዋና መለያ ዓርማ ሆኖ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ኖሯል። ‘’የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለህብረብሔራዊነት አንድነትና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው!’’ በሚል መሪ ቃል የተከበረው የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በኮሚሽናችን ሰራተኞች በድምቀት ተከብሯል። በዕለቱ የኢትዮጵያ ባንዲራ በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የተሰቀለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርም በሠራተኛው ተዘምሯል። መልዕክት ያስተላለፉት ክቡር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ሰንደቅ ዓላማችን የማንነትና የክብራችን መለያ ኩራታችን፣ ሲዘከርም የሚኖር ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች አገር እንደመሆኗ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት እንደተምሳሌት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለም በነጻነት ምልክትነት ሰንደቅ ዓላማቸው አድርገው ይጠቀማሉ።