በጅጅጋ ከተማ የሰላም ምክክር ተደረገ!

የሰላም ሚኒስቴር ከሶማሌ ክልል ጋር በመተባበር በጅጅጋ ከተማ ነሀሴ 22 እና 23/2015 ዓ/ም ባዘጋጀዉ የሰላም ምክክር መድረክ የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን አመራሮች ተሳትፈዋል።
የሰላም ምክክሩ በየሶስት ወሩ በየክልሉ በዙር የሚደረግ ሲሆን በመድረኩም የፌደራል ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሰላምና የፀጥታ ተቋማት አመራሮች ይሳተፋሉ።
በጅጅጋ ከተማ የተካሀደዉ 6ኛዉ ሲሆን በመድረኩም የሰላም ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ፣ ትግራይን ጨምሮ የ12 ክልሎችና የ2ከተማ አስተዳደሮች የሰላምና ፀጥታ ቢሮዎች የ2015 አፈፃፀምና እና የ2016 ዕቅድ ቀርቦ ምክክር ተደርጓል።
የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ብ/ጀነራል ደርቤ መኩሪያ በመድረኩ ኮሚሽኑ በ2015 ዓ/ም ያከናወናቸውን የዝግጅት ምዕራፍ አፈፃፀም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የ2016 የትኩረት መስኮች እና ከሰላም ሚኒስቴርና DDR ከሚካሄድባቸው የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮዎች የሚጠበቁ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስተዉ ለተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጎንዮሽ ዉይይቶችም ተካሂደዋል።
በመድረኩ መክፈቻ የሶማሌ ክልል ር/መስተዳድር ክቡር ሙስጠፌ መሀመድ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን መድረኩን የሰላም ሚኒስትሩ ክቡር ብናልፍ አንዷለም መርተዉታል። ቀጣይ የምክክር መድረኩ አዘጋጅ ጋምቤላ እንዲሆን ተወስኖ ዉይይቱ ተጠቃሏል።