“የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሰራተኞች የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት መዘጋጀት ይገባቸዋል” የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይህደጎ “።

የኮሚሽኑ ሰራተኞች በፌዴራል ስርዓት ዉስጥ እንደሚሰራ ተቋም ሰራተኞች እና ከተሰጠዉ ታላቅ አገራዊ ተልዕኮ አኳያ በሚኖር ሚና ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ለቀጣይ የኮሚሽኑ ተልዕኮ ማዘጋጃ የአንድ ቀን ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የሥልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይህደጎ ’’የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም ኮሚሽኑ ሰፊ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች አከናውኗል ካሉ በኋላ በሚቀጥሉት ወራትም የተቀናጀና ሰፊ ተልዕኮ የሚጠይቅ ስራ የሚጠብቀን በመሆኑ ሁሉም ሰራተኞች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እና በቁርጠኝነት ለመወጣት መዘጋጀት ይገባቸዋል” በማለት ገልጸዋል፡፡

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ተግባራት ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ያነሱት አቶ ተስፋዓለም በዋናነትም የዲሞቢላይዜሽን ማዕከላት ልየታ፣ የምዝገባ አፕልኬሽ ማበልጸግና የቅድመ-ሙከራ ስራዎች፣ የስልጠና ሰነዶች ዝግጅትና የአሰልጣኞች ስልጠና (ToT) መስጠቱን አንስተዋል፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የብቃትና የሰው ሃብት አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አቶ ግዛቸው መኩሪያው በበኩላቸው ሥራዎችን በውጤትና በስኬት ለማጠናቀቅ የሰው ሃብት ስምሪትና ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር የተቋሙን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋኦ አለው ካሉ በኋላ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች መንግስት ያወጣቸውን የሰው ሀብት አስተዳደር አዋጆችን አውቀው መተግበር ይገባቸዋል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው የሰው ሀብት ስምሪትና የስራ አፈጻጸም ምዘና፤ የሥራ ውል አስተዳደር፣ የስራ ሰዓትና ፈቃድ፣ የስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት፣ የሰራተኞች መብትና ግዴታዎች በስልጠናው ውይይት ተደርጎባቸው ለቀጣይ ሥራ መነቃቃት ተፈጥሮ ተጠናቋል፡፡