የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በመቀሌ ሲያካሂድ የነበረውን የተሃድሶ የአሰልጣኞች ስልጠና አጠናቀቀ።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ የሳይኮ ሶሻልና የሲቪክ ተሃድሶ የአሰልጣኞች ስልጠና አጠናቀቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከሰኔ 03/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ለአሰልጣኞች ሥልጠና በተዘጋጁ ሁለት ሰነዶች ላይ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡

በምክክሩ መድረኮች የተሰጡ አስተያቶችና ግብዓቶችን በማካተት ከክልሉ ለተውጣጡ ከ50 ለሚበልጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ውጤታማ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቶ በቀጣይ ተግባራትም ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ተጠናቋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው በተሃድሶ ፕሮግራም ትግበራ ወቅት የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ የተቀናጀ የሥነ-ልቦና ድጋፍና የሲቪክስ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል፡፡

ይህ ትልቅ ተልዕኮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር ካልተሰራ በስተቀር በተናጠል ጥረት እንደማይሳካ ጠቁመው አሰልጣኞች በሥልጠናው ሂደት ለሚኖራቸው ከፍተኛ ሀገራዊ ተልዕኮ ተገቢውን ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ አሳስበዋል፡፡ ለተሃድሶ ፕሮግራሙ ስኬት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እያደረገው ላለው ያልተቆጠበ ድጋፍ አመስግነው ወደ ፊትም ቅንጅቱና ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል::