የቻይና መንግስት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የቻይና ኢምባሲ ኢኮኖሚክ ካውንስለር ከሆኑት ዶክተር ያንግ ጋር በጽ/ቤታቸዉ ምክክር አድርገዋል።

ኮሚሽነር ተመስገን ከዶክተር ያንግ ጋር ባደረጉት ዉይይት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለመወጣት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።

በኮሚሽኑ የታቀዱ ተግባራት ከፍተኛ ሐብት፣ ቅንጅትንና ትብብርን የሚጠይቁ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ለፕሮግራሙ ስኬት የቻይና መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ዶክተር ያንግ በበኩላቸው የቻይና መንግስት ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለዉን ዘርፈ-ብዙ የሰላምና የልማት ስራዎች በመደገፍ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን አስታዉሰዉ ኮሚሽኑ በቀጣይ የሚተገብረው የዲሞብላይዜሽን እና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም በታቀደው ጊዜ እንዲሳካ የበኩላቸውን ድጋፍ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።