የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ተራድኦ ድርጅት (Unicef) ከብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር የተጀመሩ ትብብሮችን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁነቱን ገለጸ፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በአለም አቀፍ የዩኒሴፍ የህጻናት ጥበቃ ዳይሬክተር ሸማ ሰን ጉፕታ ጋር በጽ/ቤታቸዉ ምክክር አድርገዋል።
ኮሚሽነር ተመስገን የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለመወጣት እንዲቻል የተዘጋጀዉን የቀድሞ ተዋጊዎች ዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም አፈፃፀም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የስራ እቅዶችን ለዳያሬክተሯ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ዩኒሴፍ ከዚህ በፊት ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ ላደረጋቸው ድጋፎች አመስግነው በቀጣይ ፕሮግራሙና ፕሮጀክቶች በታቀደዉ መሰረት እንዲሳካ ትብብሩና ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነር ተመስገን ጠይቀዋል።

ዳያሬክተሯ በበኩላቸዉ ኮሚሽኑ ተልዕኮዉን ለመወጣት በያዘው ፕሮግራም ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና ልዩ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተጎጂ፣ወጣት ሴትና ወንድ የቀድሞ ተዋጊዎችን ታሳቢ አድርጎ እየሰራ መሆኑ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ አያይዘውም ፕሮግራሙ በስኬት እንዲከናወን ዩኒሴፍ በተለይ በዘላቂነት የማቋቋም ድጋፍ ላይ ትኩረት በማድረግ ኮሚሽኑ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።