የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወካዮች ጋር በDDR አተገባበር ዙሪያ በጋራ ለመስራት ምክክር ተካሄደ፡፡
(አዳማ ታህሳስ 12 ቀን 2017ዓ.ም ብ/ተ/ኮ) የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወካዮች ጋር ወደፊት ለማከናወን ስለታቀደው የDDR አተገባበር ዙሪያ በአዳማ ከተማ ምክክር አካሂዷል፡፡
የምክክሩ ዋና ትኩረት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በቀጣይ በክልሉ ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞብላይዜዝ ለማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል በጋራ ለመስራትና በስኬት ለመፈፀም የጋራ እቅዶችን ያካተተ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ አጠቃላይ የኮሚሽኑን እቅድ፣ የፕሮግራሙን ይዘት፣ የአተገባበር ስልትና የባለድርሻ አካላት ሚና በኮሚሽኑ የዲሞብላይዜሽ ዳይሬክተር በሌተናል ኮሌኔል ጎሳዬ ጥላሁን ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል፡፡
የመስክ የምልከታ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ የDDR ፕሮግራሙን በክልሉ በሚገኙ በተመረጡ የዲሞብላይዜሽን ማዕከላት ውስጥ የሚጀምር መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡
ለፕሮግራሙ ስኬት የክልሉ ህዝብና መንግስት እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት በምክክሩ ተሳትፈዋል፡፡