የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል በሚያስችሉ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት ዙሪያ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ መስተዳድርና ከተለያዩ የፌዴራልና ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመቐሌ ከተማ ምክክር እያደረገ ነው፡፡
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የትግራይ ክልል ጊዚያዊ መስተዳደር ምክትል ፕሬዘዳንት ሌ/ጀኔራል ታደሰ ወረደ በክልሉ የሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት ለመቀላቀል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲሳካ የክልሉ ጊዚያዊ መስተዳድር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚነሽር አቶ ተመስገን ጥላሁን በመክፈቻ ንግግራቸዉ በሰላም ስምምነቱ መሠረት በትግራይ ክልል ከሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎች ውስጥ በመጀመሪያው ዙር የተለዩትን ዲሞቢላይዝ በማድረግ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀልና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያስችሉ የቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንዳሉ ጠቅሰው ይህ መድረክ ይህንኑ በጋራ ለመገምገምና በቀጣይ ተግባራት ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት ብሄራዊ ተሀድሶ ቦርድ አባል ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳዔ በበኩላቸው ለፕሮግራሙ ስኬት በየደረጃው የምንገኝ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚሁ መድረክ የአፍሪካ ህብረት የሞኒተርንግና ቬሪፊኬሽን ሚሽን ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ስተፍን ራዲያንና በበኩላቸው ለስራው ስኬታማነት የቡድኑ አባላት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል። መድረኩ ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል መስሪያ ቤቶች፣ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ መስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ሲሆን የዲሞቢላይዜሽን ማእከላት ጉብኝትን በማድረግ ይጠናቀቃል ፡፡