የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በDDR አተገባበር ዙሪያ ከህብረተሰብ ተወካዮች ጋር መከረ

(አክሱም ታህሳስ 2 ቀን 2017ዓ.ም ብ/ተ/ኮ) የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል እያከናወነው ባለው የDDR አተገባበር፣ ያገጠሙ ተግዳሮቶችና የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ በአክሱም ከተማ ምክክር አካሂዷል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ እንደገለጹት የቀድሞ ተዋጊዎችን የዲሞብላይዜዝ የማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ በቀጣይ በአድዋ ማእከል የሚጀምር መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ስኬት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የኮሚሽኑን እቅድ፣ የዲሞብላይዜሽን አተገባበር ሂደት ያቀረቡት ሌተናል ኮሌኔል ጎሳዬ ጥላሁን እንደገለፁት እስከ ዛሬ ባለው ክንውን በእዳጋ ሀሙስና መቀሌ መለስ ካምፓስ አምስት ሺህ የሚጠጉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ተቀብሎ የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን 3500 የሚሆኑት ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል፡፡ 1500 የሚሆኑት በማዕከላት ውስጥ የተሃድሶ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ በፕሮግራሙ እየተሳተፉ ካሉት 30 በመቶ ሴቶች ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የማዕከላዊ ትግራይ አርበኞች ኮሚሽን ምክትል ሃላፊ ኪሮስ ሃይለ በበኩላቸው የተጀመረውን DDR ትግበራ ከኮሚሽኑና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ገር በመቀናጀት በውጤት እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግለዋል፡፡

በምክክሩ ወቅት የብሔራዊ ተሃድሶ ሂደት፣ የዲሞብላይዜሽን አተገባበር ሂደት፣ የተገኙ ውጤቶችና በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በምክክሩ የአፍሪከ ህብረት ተወካዮች፣ የኮሚሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ከማዕከላዊ ትግራይ ዞን፣ አድዋ ከተማ፣ ከአክሱም ከተማና አድዋ ወረዳ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡