የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የ2016 አፈጻጸም እና 2017 በጀት አመት እቅድ ላይ ውይይት አካሄደ።
የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመራር እና ሰራተኞች 2016 በጀት አመት በኮሚሽኑ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት አፈጻጸም አጠቃላይ ግምገማ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ በበጀት አመቱ የተገኙ መልካም ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተዳሰዋል፡፡ የ2017 ዓ.ም የትኩረት መስኮች፣ ግቦችና ዋና ዋና ተግባራት ላይም ውይይት ተደርጓል።
በ2016 ለDDR ኘሮግራም ትግበራ ዝግጅት ምዕራፍ በአመቱ የተከናወኑ ዋና ዋናዎቹ የፕሮግራምና ዝርዝር ፕሮጀክቶች ከነማስፈፀሚያ ስርዓቱ ጋር መቅረፅና የአቅም ግንባታ ስራዎች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች፣ የዲሞቢላይዜሽን ማእከላት መረጣ፣ የምዝገባ ሶፍትዌር ማበልጸግና መሞከር፣ የስልጠና ሰነዶች ዝግጅትና የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ፣ የሎጅስቲክስ አቅርቦት በሚፈለገው መጠንና ጥራት ለማግኘት ጥናት መሰራቱ፣ ሰፊ የአጋርነትና የትብብር ስራዎች መሰራታቸዉ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መቋቋሙና በሰው ሃይል መደራጀቱ በጥንካሬ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለዝግጅት ስራዎች መከናወን የተሀድሶ ቦርድ የስትራቴጂክ አመራርና ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርም ተግልጿል።
በዚህም በሚቀጥሉት ወራት የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል አብዛኛው እና ወሳኝ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ስኬታማ የአፈጻጸም ሆኖ ተገምግሟል፡፡
የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሟላ ሁኔታ ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የገንዘብና ሀብት አቅርቦት እጥረት፣የተቋም ሰው ሃይል በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላትና የፕሮግራሙ ውስብስብ ባህሪያት እንዲሁም ዘርፈ-ብዙ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብርን የሚጠይቅ በመሆኑ ስራውን ለመጀመር የነበሩ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተብራርቷል፡፡
በአጠቃላይ ሲገመገም የ2016 በጀት ዓመት ኘሮግራሙ፣ኘሮጀክቶችን ከማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ጋር የመጨረሻ ቅርጽ ይዞ የጸደቀበት እንዲሁም ለመጀመሪያውን ዙር የተያዘውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ የማድረግና መልሶ የማቋቋም ስራ ከኮሚሽኑ የሚጠበቀውን አስፈላጊውንና አብዛኛውን የመስክ ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቀበት አመት መሆኑን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት አመትም የተያዙ እቅዶችን ለመፈጸም መንግስት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ የመጀመሪያዉን ዙር ስራ ለመከወን የሚያስችል የመነሻ አንድ ቢሊዮን ብር የኘሮግራም በጀት መመደቡንም ይፋ አድርገዋል፡፡ ስለሆነም ቀሪ ተግባራትን በፍጥነት በማከናወን ፕሮግራሙን በስኬት ለማጠናቀቅ መላው የኮሚሽኑ ሰራተኛ በትጋት በመስራት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ያሳሰቡት ኮሚሽነር ተመስገን የተመደበልን በጀት ከለጋሽ አካላት ከምናገኘው ድጋፍ ጋር በማቀናጀት ስራችንን በብቃት ለመወጣት በምናደርገው ርብርብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡