የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግ የተመረጡ ማዕከላትን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተረከበ።(መቀሌ ነሐሴ 4/2016ዓ.ም)

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል የሚያገለግሉ ሶስት ማዕከላትን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በዛሬው እለት መረከብ ከእዳጋ ሀሙስ(ማዕከል 1) ጀምሯል፡፡

በርክክቡ ወቅት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደገለጹት የማእከላቱ ርክክብ የDDR ፕሮግራም ወሳኝ የትግበራ ምእራፍ ላይ ለመድረሱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው የቀድሞ ተዋጊዎችን ተቀብለን ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀላችን በፊት በመለየት፣ ምዝገባ በማካሄድ፣ የሳይኮ ሶሻልና የሲቪክ ስልጠና ለመስጠት፤ እንዲሁም ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው የሰላም እና የልማት አጋር እንዲሆኑ ለማስቻል የተያዘውን የዲሞቢላይዜሽንና የተሀድሶ ኘሮጀክቶች የመተግበሪያ ማዕከላትን ተረክበናል ብለዋል፡፡ ይፋዊ ቅበላና የፕሮግራሙ ማስጀመር ስራ በቅርቡ እንደሚከናወን ጠቅሰውም ይህን ፕሮግራም ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካይ ገብረ ገብረጻድቃን ማዕከላትን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው የDDR ፕሮግራም ትግበራ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ሲሉ ድጋፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በበኩላቸው ርክክብ የሚደረግባቸው ሶስት ማዕከላት መሆናቸውን ጠቅሰው ማዕከላቱን ከክልሉ ተረክበን በማደስና በማስተዳደር የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ በማድረግ ለሰላም፣ ለልማትና ራሳቸውን በዘላቂነት ለማቋቋም ለምንሰራው ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ ጸጥታ ሀይሎች ለማእከላቱ ተገቢውን የጸጥታ ጥበቃና የስራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

በርክክቡ ወቅት ጥሪ የተደረገላቸው የትግራይ ክልልና የዞን አመራሮች፣ የጸጥታና ደህንነት የስራ ሃላፊዎች፣ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች ቡድን መሪ ጀነራል ስቴፈን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው የማህበረሰብ ተወካዮችም ተገኝተዋል፡፡