የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ለመደገፍ የአሜሪካ መንግስት ዝግጁ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በድጋሚ አረጋገጡ::
ክቡር የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ኧርቭን ጆስ ማሲንጋ ጋር በጽ/ቤታቸዉ ምክክር አድርገዋል።
ክቡር ኮሚሽነር ተመስገን ከአምባሳደር ሚስተር ማሲንጋ ጋር ባደረጉት ዉይይት የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለመወጣት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት አብራርተዋል።
አጋር አካላት እስካሁን እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦና ትብብር የሚደነቅ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ የአሜሪካን መንግስትም ለፕሮግራሙ ድጋፍ አጋርነት ማሳየቱን አመስግነው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ክቡር አምባሳደር ማሲንጋ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ተልዕኮዉን ለመወጣት እያደረገ ያለዉን ሁሉን አቀፍ ጥረት አድንቀዉ በቀጣይ የዲሞብላይዜሽን እና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራሙ በታቀደዉ መሰረት እንዲሳካ የአሜሪካን መንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።