የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በሳይኮ ሶሻልና የሲቪክ ተሃድሶ ስልጠና ሰነዶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መቐሌ ምክክር እያካሄደ ነው፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ የሳይኮ ሶሻልና የሲቪክ ተሃድሶ ስልጠና ሰነዶች ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው እንደገለጹት የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግ ሊኖር የሚችለውን የስነ-ልቦናና ማህበራዊ መስተጋብር ሊያዳብሩ እንዲችሉ እንዲሁም ለሀገራቸው ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኛነት ነፃ የሆኑ ሰነዶች እንዲዘጋጁ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ለውይይቱ በቀረቡት ሰነዶች ይዘት ላይ ሰፊ ግብዓት መስጠትና ማካተት ኮሚሽኑ እየተገበረ ላለው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው ያሉት ጀነራል ደርቤ ኮሚሽኑ ብቁ ባለሙያዎችን በመመደብ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴርና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ሁለቱን ሰነዶች በማዘጋጀት ለተሃድሶ ስልጠና ዝግጁ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያው መስተዳደር የማሕበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሃላፊ ጀነራል ተክላይ አሸብር በበኩላቸው የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና መልሶ ለመቋቋም የትግራይ ክልል በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ ነው፡፡ ሰነዶችን በውይይትና በምክክር በማዳበር በጋራ እንተገብረዋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሰነዶቹ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ተጨማሪ ግብዓት ለማካተት የተቻለ ሲሆን በዛሬዉ ዕለት በሳይኮ ሶሻል ተሃድሶ ስልጠና ሰነድ ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት የተጀመረ ሲሆን በሲቪክ የተሃድሶ ሰነድ ላይም የአሰልጣኞች ስልጠና በሚቀጥሉት ቀናት መሰጠት ይጀመራል፡፡