የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነርና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚ/ር ዴኤታ ተወያዩ፡፡

ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም (ብ/ተ/ኮ)፣ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የዲሞብላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ዘርፍ  ም/ኮሚሽነር  ክቡር ብ/ጄ ደርቤ መኩሪያ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ ጋር ለቀድሞ ተዋጊዎች ስለሚሰጥ የሙያና ክህሎት ስልጠና እና መልሶ ማቋቋም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ብ/ጄ ደርቤ መኩሪያ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እስከአሁን ያከናወናቸውንና እያከናወናቸው የሚገኙ ዋና ዋና ተግባራትን በዝርዝር በማንሳት ኮሚሽኑ የሚገኝበት አሁናዊ ሁኔታን ገልጸው ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮውን በላቀ ደረጃ ለመወጣት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብበር እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በተለይ በዲሞብላይዜሽን ሂደት ከቀድሞ ተዋጊዎች የክህሎት ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን ብቻ በመለየት በሚመርጧቸው መስኮች አጭር የሙያ ስልጠና መስጠትና ለመልሶ መቋቋም ዝግጁ የማድረግ ተግባራት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅትና በኃላፊነት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤታቸው እንደ አንድ ቁልፍ ባለድርሻ አካል የክህሎት ስልጠና የሚሰጡ ተቋማትን በመለየት፣ የስልጠና ማንዋሎችን እና አሰልጣኞች በማዘጋጀት ረገድ የሚጠበቅበትን ሁሉ ከኮሚሽኑ ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡   

በመጨረሻም ቀጣይ ስራዎችን ለመምራት የሚያስችል የጋራ ዕቅድ እንዲዘጋጅ እንዲሁም በኮሚሽኑ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ በታቀዱ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ በመምከር እና ሁሉም የድርሻውን መውሰድ እንዲችል በተለዩ እና መግባባት በተደረሰባቸው ተግባራት ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ በመፈራረም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡