የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ!!
የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ በማድረግና መልሶ በማቋቋም የሰላምና የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በትብብርና አጋርነት ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት ክቡር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር ኢንጂነር መላኩ ይዘዘው ሲሆኑ በስነ ስርዓቱ ላይ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በአገራችን በድህረ-ግጭት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ እና ዋነኛው በግጭቱ ወቅት ከመንግስት ጋር ሲፋለሙ የነበሩ ኃይሎች በሰላም ስምምነት መሰረት ትጥቃቸውን የሚፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ በማድረግና መልሶ በማቋቋም የአገሪቱ ሰላምና ልማት አካል እንዲሆኑ ማስቻል ሲሆን ይህም ኃላፊነት የተሰጠው ለብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ነው፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ የኮሚሽኑ ተልዕኮዎች እንዲሳኩና በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በአጋርነትና ትብብር የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባበርና በማቀናጀት የፋይንናስ፣ የማቴሪያልና የቴክኒክ ድጋፎች የሚያደረጉበትን ምቹ ምህዳር በመፍጠር የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ሚና ለመጫወት የሚያስችል ማዕቀፍ መሆኑ ታምኗል፡፡ በዚሁ ወቅት ስምምነቱን መነሻ በማድረግ የ2016 በጀት ሁለተኛ ግማሽ ዓመት በጋራ የሚሰሩ ስራዎች ተለየተው የጋራ መግባባትም ተፈጥሯል፡፡