ኮሚሽኑ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገመገመ!

ኮሚሽኑ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን ያካሄደው ከመስከረም 24 – 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲሆን፣ የሦስቱም ስራ ዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል። በግምገማው የተከናወኑ ስራዎች፣ በዕቅዱ መሰረት ያልተከናወኑ ስራዎች፣ በአፈጻጸም ሂደት የተገኙ ልምዶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የቀጣዩ ጥቅምት ወር የዕቅድ የትኩረት መስኮች በኮሚሽነር ጽ/ቤት በስትራቴጂክ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

ስብሰባውን የመሩት ክቡር ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከተከናወኑ ተግባራት ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበት እንዲሁም እጥረቶችን ለይቶ በማተኮር፣ ራስን በተለያዩ አግባቦች በማብቃትና ከመልካም ተሞክሮዎች በመማር በቀጣይ ጊዜያት እያሻሻሉ በመተግበር ዕቅዶችን ሙሉ በሙሉና በጥራት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በግምገማው ወቅት የተዘጋጀ ‘’ረቂቅ የቀድሞ ተዋጊዎች፣ የዲሞቢላይዜሽን፣ የተሃድሶ ስልጠናና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ማንዋል’’ በዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ዘርፍ ለውይይት ቀርቦ ገንቢ ግበዓቶች ተሰጥተውበታል። በተሰጡት ግበዓቶች ዳብሮና ለማኔጅመንት ቀርቦ እንዲጠናቀቅና ስራ ላይ እንዲውል ክቡር ኮሚሽነር አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ ቀደም ሲል ለማኔጅመንቱ የቀረበውም ረቂቅ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነድ በመጪው ሳምንት በግበዓቶች ዳብሮ እንደሚጠናቀቅና ስራ ላይ እንደሚውልም ክቡር ኮሚሽነር ጨምረው ገልጸዋል። በመቀጠልም ‘’የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ተቋማዊ የስራ ግንኙነት ስብሰባዎችና የመረጃ ልውውጥ የውስጥ አሰራር’’ በሚል ርዕስ በኮሚሽነር ጽ/ቤት በቀረበው ጽሑፍ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፣  ግበዓቶችም ተሰጥተውበታል፡፡ በግበዓቶቹ መሰረትም ሰነዱ ዳብሮ ለማኔጅመንት እንዲቀርብና ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል ክቡር ኮሚሽነር በተመሳሳይ መመሪያ ሰጥተዋል። በቀጣዩ የግምገማ ዕለትም ለእርስ በርስ መማማሪያ እንዲሆን ‘‘ለውጥ፣ የለውጥ ባህሪያትና ተቋማዊ ባህል’’ በሚል ርዕስም በኮሚሽነር ጽ/ቤት ጽሑፍ ቀርቦ ሃሳቦች ተንሸራሽረውበታል፡፡ ለግል ህይወትም ለስራም በሚረዳ መልኩ ተገቢ ግንዛቤ ተወስዶበታል።

በማጠቃለያም ክቡር ኮሚሽነር በግምገማው ዙሪያ አጠቃላይ አስተያየት፣ ምክር፣ አቅጣጫና ማሳሰቢያዎችን ሰጥተው ለቀጣይ ስራም ሰራተኛውን በማበረታታት ግምገማው በዚሁ ተጠናቋል፡፡