ክቡር ኮሚሽነር ከመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ጋር ተወያዩ!

የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ  ህዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሚስተር ቱርሃን ሳለህ  ጋር በጽ/ቤታቸዉ ምክክር አድርገዋል።

የውይይቱ ዋነኛ ምክንያትም ሚስተር ቱርሃን ባለፉት አራት ዓመት ተኩል በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ቆይታ አጠናቀው የሚሰናበቱ በመሆናቸው ነው።

የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ሚስተር ቱርሃን ለአገራችን ሰላም ግንባታ በአጠቃላይና በተለይ ደግሞ ለብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ተልዕኮዎች ስኬት በሰው ሀይል ልማት ፣ በተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራር  ዝርጋታ ፣ በፕሮግራምና ፕሮጀክት ዝግጅት እንዲሁም በቢሮ መገልገያዎች አቅርቦት ላደረጉት አስተዋፅዖ በኮሚሽኑና በራሳቸው ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበው በቀጣይ በሚኖራቸው ተልዕኮም ስኬታማነትን  ተመኝተውላቸዋል።

በተመሳሳይ ሚስተር ቱርሃን በበኩላቸው ከኮሚሽኑ ምስረታ ጀምሮ የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከዩ.ኤን.ዲ.ፒና ከሌሎች አጋሮች ጋር  በትብብር እና አጋርነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የኮሚሽኑ ተልዕኮ እንዲሳካ እያደረጉ ያለውን ውጤታማ ተግባራት አድንቀው ይህ ትልቅ አገራዊ ተልዕኮ በእርሳቸው የአመራር ዘመን እንዲሳካ ልባዊ ምኞታቸውን ገልፀዋል ።

በዚህ ዉይይት ሚስ ቻሩ ቢስት በዩ.ኤን.ዲ.ፒ ኢትዮጵያ የፕሮግራም ዘርፍ ምክትል እና ሚስተር ባዝል ማሰይ የDDR አማካሪ ተገኝተዋል ።