አዲስ ለተሾሙት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነር የስራ ርክክብ ተከናወነ፡፡

አዲስ የተሾሙት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ከቀድሞው ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የተቋሙ የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት የስራ ርክክብ በማድረግ ዛሬ ስራቸውን በይፋ ጀምረዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ዶክተር አትንኩት መዝገበም ስራቸውን በዚሁ ስነ ስርዓት ለአዲሱ ምክትል ኮሚሽነር ተስፋአለም ይህደጎ አስረክበዋል፡፡

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በርክክቡ ላይ እንደገለጹት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት ባሳለፍነው አንድ አመት ተቋሙን በማቋቋምና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና የጋራ መግባባት በመፍጠር፣ የሀብት ማሰባሰብ ስራዎችን በመስራት ከለጋሽ አገራትና ድርጅቶች ድጋፍና እገዛ በማግኘት የመጀመሪየውን ዙር የዲሞቢላይዜሽን ስራ ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አብስረዋል፡፡ ተቋሙ አሁን የደረሰብት ደረጃ እንዲደርስ አብረዋቸው ለተጓዙት የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበው ለአዲስ አመራሮች የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል መስሪያ ቤቱ የተቋቋመለትን አላማ ለማሳካት እንዲችሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑን አጠቃላይ የስራ ክንውን፣ እቅድና ትኩረት የሚሹ ጉዳየችን እንዲያብራሩ የተጠየቁት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የኮሚሽነር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሻንቆ ደለለኝ “ከሰላም ብዙ እናተርፋለን ከግጭት ብዙ እናጣለን፡፡ የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ፣ በመሰረታዊ የስነ-ልቦናና የክህሎት ስልጠና የታገዘ፣ አምራችና ማህበረሰቡን ሊጠቅም በሚችል ዘርፍ ላይ በማተኮር የቀድሞ ተዋጊዎችን ማቋቋም ጊዜ የማይሰጠው ነው” ሲሉ ለተገኙ ኮሚሽነሮችና የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች አብራርተዋል፡፡

የኮሚሽኑን ስራ ለማስፈጸም ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት አቶ ሻንቆ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት በተለይም ከለጋሽ አገራት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ በግል ዘርፉ ላይ ከተሰማሩ አካላትና ከሲቪክ ድርጅቶች ጋር በማቀናጀት መስራት እንደሚያስፈልግ አስታውሰዋል፡፡ ለተልዕኮው ስኬትም ዘርፈ ብዙ ሀብት ለማሰባሰብ  የማህበረሰብ ተኮር የኮሙኒኬሽን ንቅናቄ በመፍጠር የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት ማቋቋም ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ሲያጠቃልሉም ተቋሙ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተጽኦ ላበረከቱት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና ለዶክተር አትንኩት መዝገበ በተቋሙ ሰራተኞች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ኮሚሽነር ተመስገን ከቀረበላቸው ገለጻ በመነሳት ስለተቋሙ ለመነሻ የሚሆን የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው በቀድሞው አመራር የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠልና የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽኦ በማድረግ ተቋሙ የተሰጠውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ የማድረግና በዘላቂነት በማቋቋም የአገሪቱ የሰላምና የልማት ሂደትና ውጤት ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ተልዕኮ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡