“አብዘሃኛው ትጥቅ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሃይል ትጥቁን በመፍታት ወደ ሰላም ፊቱን አዙሯል” ሲሉ አቶ አሻድሊ ሃሰን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገለፁ።

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጋር በጽ/ቤታቸው ውይይት አድርገዋል፡፡

ኮሚሽነር ተመስገን የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በቅድመ-ዝግጅት ስራዎች በተሻለ የመፈጸም አቅምና ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ዙር የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞብላይዝ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የስልጠና ሰነዶች ዝግጅት፣ የማዕከላት ልየታ፣ የምዝገባ አፕልኬሽ ማበልጸግና የቅድመ-ሙከራ ስራዎች፣ እንዲሁም በሳይኮ-ሶሻልና ሲቪክስ ሰነዶች ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠቱን አብራርተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች አብዛኛዎቹ ከክልሉ መንግስት ጋር በመስማማት ትጥቃቸውን በመፍታት የሰላም የመረጡ መሆናቸዉን ገልፀዋል፡፡
ክልሉ ያለውን ሀብት በሙሉ አቅሙ ለማልማት ሰላም የማይተካ ሚና ይጫወታል ካሉ በኋላ ትጥቅ በመፍታት ወደ ሰላም የመጡትን የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም አስፈላጊውን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር እንዲደረግልን ሲሉ የኮሚሽኑን ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽነር ተመስገን ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ለመወጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዉ በዚህ ረገድ በተለይም ክልሎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል ፡፡ በመሆኑም ክልሉ በራሱ አቅም የጀመረውን የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም ስራ ለመደገፍ እና በጋራ ለመስራት አቅደናል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡