ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከInitiative Africa ጋር በመተባበር ከግሉ ሴክተር ጋር የጋራ ምክክር መድረክ አዘጋጀ!
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በግሉ ዘርፍ ግንባታ ላይ ከሚሰራውና አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ከሆነው Initiative Africa ጋር በመተባበር ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. መድረክ አዘጋጅቶ ከግሉ ሴክተር ጋር የጋራ ምክክር አድርጓል። በመድረኩ ክቡር ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የግሉ ዘርፍ በሰላም ሂደቱ ግጭት በነበረባቸው ክልሎች በDDR ፕሮግራሙ የቀድሞ ተዋጊዎች ተሃድሶ ወስደው ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ በሚደረገው የተለያዩ የሳይኮ – ሶሻልና የክህሎት ስልጠናዎች እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራዎች በተያያዘም በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የግሉ ዘርፍ አባላት በፕሮግራሙ ተገቢውን ግንዛቤ ጨብጠው ጉዳት የደረሰባቸውን የሕብረተሰብ አካላትና የተቀዛቀዘውን የንግዱንና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል። ለንግዱ ማሕበረሰብ ዕድገት ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው SIDA ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት በስዊድን ኤምባሲ የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ኃላፊ Mrs. Asa Andersson ኤጀንሲው በግጭቶች መቀዛቀዝ ያሳየው የግሉ ዘርፍ እንዲነቃቃና ከራሱም አልፎ ለDDR ፕሮግራሙ የሰላም ሂደት ድጋፍ ማድረጉ ለዘርፉ ሰላማዊና የተመቻቸ ሁኔታን ስለሚፈጥርለት እገዛውን እንደሚቀጥል አሳውቀዋል። በመድረኩ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ደገላ ኤርገኖ ባደረጉት ንግግር የግሉ ዘርፍ የሰላም ሂደቱ ላይ በመሳተፍ የተቀዛቀዘውን የዘርፉን እንቅስቃሴና በስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በስነ – ልቦና ስልጠናዎች የቀድሞ ተዋጊውን በመደገፍ በሌላም በኩል በግጭቶች የተጎዳውን ማሕበረሰብ በተለያዩ አግባቦች በመደገፍ በባለቤትነት ስሜት የድርሻውን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ አሳስበዋል። በመድረኩ ተጋባዥ ሆነው የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር የሚኒስተሩ አማካሪ ወ/ት ትዕግስት ፍሰሀ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ስለተዘጋጁ የተለያዩ ፓኬጆችና ተመጋጋቢነታቸው ዙሪያ ገለጻ አድርገው ይህም DDR ፕሮግራም አንዱና በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት ድጋፍ እንደሚደረግለት ገልጸዋል፡፡ ይህም ፎረም ሊደረግ ከሚገባ ድጋፍ አንጻር እንደሚበረታታ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ ከInitiative Africa ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ዳንኤል መኮንን የግሉ ዘርፍ የተቀዛቀዘውን ስራውን አጠናክሮ ለራሱ ዕሴት ከመጨመርና ከአጋርነትና ትብብር ባሻገር የባለቤትነት ስሜት ፈጥሮ የሰላም ሂደቱ አካል የሆነውን ይህን የDDR ፕሮግራም መደገፉ የዘርፉን ስራ መደገፍ ነው ብለው አስምረውበታል፡፡ በመድረኩ የDDR መሠረታዊ ታሳቢዎችና በፕሮግራሙ የግሉ ዘርፍ ሚና ዙሪያ ሁለት ጽሑፎች በኮሚሽኑ የዘርፍ ኃላፊዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በመጨረሻም መድረኩ የመጀመሪያ እንደመሆኑ ወሳኝ ግንዛቤ የተጨበጠበትና በቀጣይ መድረኮች እየተገናኙ መመካከሩ እንዲቀጥል ለቀጣይ ስራዎችም በቅርቡ ከኮሚሽኑ ጋር የጋራ የስራ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ቀጣይ ስራ እንዲገባ ስምምነት ተደርጎ የዕለቱ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።