ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከአለም አቀፍ ለጋሽ ሀገራትና ተቋማት ተወካዮች ጋር መከረ፣

(አዲስ አበባ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ብ/ተ/ኮ) ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከአለም አቀፍ ለጋሽ ሀገራት አምባሳደሮችና ተወካዮቻቸው ጋር በቅርቡ ተግባራዊ በሚደረገው የDDR ፕሮግራም አተገባበር እና ሂደት ላይ መክሯል፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮምሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደገለጹት የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞብላይዝድ ለማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ኮሚሽኑ አስፈላጊውን አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቅሰው የመጀመሪያውን ዙር ዲሞቢላይዜሽን ስራ በትግራይ ክልል ለመጀመር የዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮግራሙን በስኬት ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኑንና ለዚህም ተገቢውን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል። የለጋሽ ሀገራት ሚናም ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ ለጋሽ ሀገራትም የበኩላቸውን ድጋፍና ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ የተሀድሶ ቦርድ አባል ሌ/ጀ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ በበኩላቸው ቦርዱ እየሰጠ ስላለው ስትራቴጂክ አመራርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለDDR ትግበራው ያለውን ቁርጠኝነትና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍና እቅድ አብራርተዋል።

በተያያዘም በመድረኩ የተገኙ የለጋሽ ሀገራት ተወካዮች እና አምባሳደሮች ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን የDDR ፕሮግራም ትግበራ ለሰላምና ለዘላቂ ልማት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም ድጋፍ እና ትብብር ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።