ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከሚዲያ ተቋማት ጋር ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የጋራ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል።
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከሚዲያ ተቋማት ጋር ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የጋራ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል። መሰል የምክክር መድረኮችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያደረግን እንገኛለን ያሉት ኮሚሽነር ክቡር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የተሃድሶ ፕሮግራሙ ስኬታማ እንዲሆን የሚዲያ ተቋማት አጋርነትና ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል። በኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች በቀረቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፎች ሚዲያ አካላት
- ስለፕሮግራሙ ምንነት፣ አስፈላጊነትና ፋይዳ ተገቢውን ግንዛቤ መጨበጥ፣
- ፕሮግራሙን በኃላፊነትና በባለቤትነት ስሜት የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት እንዲረዱና እንዲደግፉት መስራት፣
- በፕሮግራሙ አፈፃፀሞች፣ ውጤቶችና ተግዳሮቶች በመረጃዎች በመመስረት ለህዝብና ባለድርሻ አካላት ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል። የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋሙ ሂደት ኮሚሽኑ የተለያዩ ስትራቴጂዎችንና መመሪያዎችን እያዘጋጀ ያለ መሆኑን የገለፁት ክቡር ኮሚሽነር ከውጭ ለጋሽ ባለድርሻ አካላት ባሻገር ውስጣዊ ትስስርና መደጋገፍን ለማጠናከር በአገራችን ካሉ የውጭና አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከግሉ ሴክተር፣ የሙያ፣ የፆታ፣ የሐይማኖት ማህበራት፣ ከሚዲያ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ አዋጪ በመሆኑ ለሚዲያ ተቋማቱ የአጋርነትና ትብብር ጥሪ አድርገዋል። በቀረቡ ጽሑፎችም በተሃድሶ ፕሮግራሙ ታሳቢዎች ዙሪያ ተሳታፊዎቹ ተገቢውን ግንዛቤ ጨብጠዋል። በተደረጉ ውይይቶችም ኮሚሽኑ ዋና ስራውን ሊጀምር እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት መድረኩ መዘጋጀቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው፣ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና፣ ከተሃድሶ ፕሮግራሙ አፈፃፀም አንፃር ስለሽግግር ፍትህ ታሳቢዎች፣ ፕሮግራሙን ሊፈታተኑ ስለሚችሉ ብቅ ጥልቅ ስለሚሉ ግጭቶች፣ ለቀድሞ ተዋጊዎች ዘላቂ ገቢ ከመፍጠር አንፃር ታሳቢዎች፣ የህወሃትና የምርጫ ቦርድ ሁኔታ፣ የቀድሞ ተዋጊዎች ትርጓሜ በሁሉም ክልሎች ላይ አተገባበር በተለይም ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ይዋጋ ስለነበረው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት፣ በማህበረሰባቸው ላይ ጥቃት አደረሱ ስለተባሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች፣ የቀድሞ ተዋጊዎች ልየታ ታሳቢዎች፣ ስለኮሚሽኑ የስራ ዘመን ማጠር ስጋት፣ ከሚዲያ አካላት ባሻገር ስለአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት ተቋማትና አባቶች የአስታራቂነት ሚና ከተሳታፊዎች ሰፊ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው በክቡር ኮሚሽነር በኩል በደንቡ መሠረት ብሔራዊ ተሃድሶ ምክር ቤት ቢቋቋምም የሌሎች አካላት መካተት ሲታመንበት የሚታቀፉበት አግባብ ስለመኖሩ፣ በተሃድሶ ፕሮግራሙ የታቀፉ የቀድሞ ተዋጊዎችም ሆኑ ሌሎች ያልታቀፉ ግለሰቦች ወንጀል መፈፀማቸው ከተረጋገጠ ፀድቆ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ በሚጠበቀው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ፣ የሰላም ስምምነቱ በመንግስትና ተዋጊ በነበሩ ኃይላት የጋራ ይሁንታና የፖለቲካ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የተገኘ ስለመሆኑ፣ ማህበረሰባቸውን እያጠቁ ያሉ ታጣቂዎችን ለማሳረፍ በተቻለ ፍጥነት ፕሮግራሙን በመተግበር የታጣቂዎችን ተስፋ በአዎንታዊነት ከፍ ማድረግና ሰላም ለመጠማቱ በተደጋጋሚ እየገለፀ ያለውን የቀድሞ ተዋጊ በቀጣይነት ሰላሙ ላይ አትኩሮ መስራት እንደሚገባ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን በመለየት ረገድ መከላከያና ክልሎች በመግባባት አጥርተው የጨረሱት ስለመሆኑ፣ ከትርጓሜ ጋር በተያያዘ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በኮሚሽኑ ፕሮግራም የማይታቀፉና ከኮሚሽኑ ውጪ ሌላ ፕሮግራም የተዘጋጀላቸው ኮሚሽኑ የማይመለከተው ስለመሆኑ የኮሚሽኑ ማዕቀፍ መንግስትን ሲወጉ የነበሩ የቀድሞ ተዋጊዎች፣ ያግዟቸው የነበሩ ሲቪሎችና የሚቀላቀሉበት ማህበረሰብ ስለመሆኑ ተገቢው ግንዛቤ እንዲወሰድ፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሐይማኖት አባቶችን ማሳተፉ ተገቢ ስለመሆኑ በመግለፅ ሰፉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሚዲያ አካላቱ በውይይቱ ተገቢ ግንዛቤ መጨበጣቸውን፣ እነርሱን ማዕከል አድርጎ መድረኩ መዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸውና ይህም በፕሮግራሙ ዙሪያ በቀጣይ ጊዜያት በመደጋገፍ፣ በትብብር፣ በባለቤትነትና በኃላፊነት መንፈስ ከኮሚሽኑ ጋር አብረው እንደሚሰሩ አስምረውበት ውይይቱ በመግባባትና በይሁንታ ተጠናቋል።