ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ!
ኮሚሽኑ ለተሃድሶ ፕሮግራሙ ስኬት የውስጥና የውጭ አጋርነትና ትብብሮችን በማጠናከር ስራዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ከለያቸው ዋነኛ የትብብር አጋሮች መካከል አንዱ ከሆነው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ተፈራርሟል። ስምምነቱን የፈረሙት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አምባሳደር ተሾመ ቶጋና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃና ወ/ገብርኤል ናቸው።
በአገራችን የተለያዩ ክልሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞች እየተገበሩ የሚገኙ ከ4000 በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያቀፈው ምክር ቤቱ አብሮ በመስራትና በተሃድሶ ፕሮግራሙ የተለያዩ የድጋፍ ስራዎች በመሳተፍ ለሰላም ሂደቱ አስተዋጽዖ ለማበርከት ይህ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈረሙ በዋናነት የሚታይ ሲሆን፣ ከስምምነቱ ባሻገርም በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ገብቶ ውጤት ማሳየት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ክቡር ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባቀረቡት ንግግር አሳስበዋል። የምክር ቤቱ ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃና ወ/ገብርኤልም ዘርፉ ከሚጠበቅበት የድጋፍ ስራዎች አንጻር ወሳኝ ሚና መጫወት እንዲሁም ተገቢውን አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚገባና እንደሚችልም ገልጸው፣ ይህ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ የጋራ ስራ መመሪያ መነሻ ሆኖ ያገለግለናል ብለዋል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ፣ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ዳይሬክተር፣ የሁለቱ ተፈራራሚ ወገኖች የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ሚዲያዎች ተገኝተዋል።