ብሔራዊ ተሃድሶ ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን አደረገ

ብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንን በበላይነት የሚመራው “ብሄራዊ የተሀድሶ ም/ቤት” 4ተኛ መደበኛ ስብሰባውን መስከረም 2/2016 ዓ/ም ከሰዓት በኋላ በሰላም ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ አካሂዷል ።
ስብሰባዉን የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትርና የም/ቤቱ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም የመሩት ሲሆን የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንዲሁም የመከላከያ ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታዎች ተገኝተዋል ። በተጨማሪም የኮሚሽኑ የስራ ሀላፊዎች በአስረጅነት ተሳትፈዋል ።
በዚህ የዉይይት መድረክ የኮሚሽኑ የ2015 ዕቅድ አፈፃፀምና የ2016 ዕቅድ ዋና ዋና ጉዳዮች በኮሚሽኑ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ በአቶ ተስፋዬ ብርሃኑ የቀረበ ሲሆን የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ የም/ቤቱን ስትራቴጂካዊ ዉሳኔ የሚሹ ወሳኝ ጉዳዮችን ለይተዉ ለዉይይት መነሻ ካቀረቡ በኋላ ም/ቤቱ ሰፊ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት ተወያይቷል ።
በዉይይቱ ማጠቃለያ የኮሚሽኑ የ2015 አፈፃፀምና በ2016 ዕቅድ ላይ የማዳበሪያ ግብዓት ተሰጥቶት የጋራ መግባባት ተደርሷል ። በሌላ በኩልም ኮሚሽኑ ተልዕኮዉን ለማሳካት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደ ም/ቤት የጋራና የተናጠል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ መግባባት ከመደረሱም በላይ በቀጣይ የትኩረት መስኮችም ላይ መመሪያ ተሰጥቷል ።
በመጨረሻም የሚቀጥለው የም/ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በኮሚሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ለማድረግ ተወስኖ ከቀኑ በ11 ሰዓት ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቋል ።