ብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በስምምነቱ ወቅት የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማህረሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት ያሉበትን የጤና ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የጤና እና የስነ-ልቦና ድጋፍና የምክር አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸዉ ገልፀዉ ለዚሁ ተልዕኮ ስኬት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት ከመግባባት ተደርሷል ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቀድሞ ተዋጊዎች በጦርነት ወቅት የጦር ጉዳትና የስነ-ልቦና ጫና እንደሚያጋጥማቸዉ ጠቅሰዉ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት የኮሚሽኑ እና የጤና ሚኒስቴር አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ የፌደራል ተቋማት የተጋበዙ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ስምምነቱን መነሻ አድርገዉ የተዘጋጁና ለስነ-ልቦና ድጋፍና ለስልጠና የሚያገለግሉ ማሰፈፀሚያ ማንዋሎች ቀርበዉ ሰፊ ምክክር በማካሄድ ተጨማሪ ግብዓቶች ማግኘት ተችሏል፡፡