ብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እያከናወነው ላለው የDDR ፕሮግራም የእንግሊዝ መንግስት 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

መቀሌ፣ መስከረም 30/2017ዓ.ም (ብ/ተ/ኮ) የእንግሊዝ መንግስት የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞብላይዝ በማድረግ ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ለመቀላቀልና ለማቋቋም የሚያግዝ የ16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ፓወንድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታዉቋል፡፡

የድጋፍ ማእቀፉን ያሳወቁት በብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሎርድ ኮሊንስ የተመራው ልዑክ በመቀሌ በመገኘትም የብሄራዊ ተሀድሶ ቦርድ አባል ሌ/ጀ ጻድቃን ገ/ትንሳኤ እና ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንዲሁም የዩኤንዲፒ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት የቀድሞ ተዋጊዎች ዲሞቢላይዜሽን ማእከል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ኮሚሽነር ተመስገን የእንግሊዝ መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ኮሚሽኑ የDDR ዝግጅት እያገባደደ ባለበትና የመጀመሪያው ምእራፍ ትግበራ ጅማሮ ዋዜማ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማዕከላት በማስገባት የተሃድሶ ስልጠና በመስጠትና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ በመቀላቀል ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩና በዘላቂነት በማቋቋም አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡