“በጋራ እና በቅንጅት በመስራት የቀድሞ ተዋጊ ሴቶችንና የጦርነት ተጎጂ ወገኖችን መልሶ ማቋቋምና የኢኮኖሚ ጫናን ማቃለል ይቻላል፡፡” ሢስሌ ሙካሩቡጋ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ልማት ድርጅት (UN Women) ተወካይ።
የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ልማት ድርጅት (UN WOMEN) ተወካይ ሢስሌ ሙካሩቡጋ ጋር በጽ/ቤታቸዉ ምክክር አድርገዋል።
ኮሚሽነር ተመስገን ከዚህ በፊት ከድርጅቱ ጋር በቅንጅት በመስራት ዙሪያ የነበሩ ጅምሮችን አስታዉሰዋል። በቀጣይም የዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራሙ በተለይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተጎጂዎችን እና ሴት የቀድሞ ተዋጊዎችን ታሳቢ አድርጎ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ይህንኑ ሂደት ወደ ዉጤት ለመቀየር በተቀናጀ ዕቅድ አጠናክረን እንቀጥል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ተወካይዋ በበኩላቸዉ ኮሚሽኑ ተልዕኮዉን ለመወጣት ከያዘው አገራዊ ፕሮግራም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት እየሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ሲሆን በጋራ በመስራት በተለይ ሴቶችን ካለባቸው ጫና ማላቀቅ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ፕሮግራሙ በስኬት እንዲከናወን ድርጅታቸው በተለይም በዘላቂነት የማቋቋም ድጋፍ ላይ ትኩረት በማድረግ ከኮሚሽኑ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በድጋሚ አረጋግጠዋል።