በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ከብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር ተወያዩ
የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ከአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሶፌ ፍሮም ኢመስበርግ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
ኮሚሽነር ተመስገን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞብላይዝ የማድረግና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የመቀላቀል ቅድመ-ዝግጅት መጠናቀቁን ለአምባሳደሯ አብራርተዋል፡፡ በተለይም የቀድሞ ተዋጊዎችን የመለየት፣ የሳይኮ-ሶሻልና የሲቪክስ ተሃድሶ ስልጠና ሰነዶች ዝግጅት፥ የአሰልጣኞች ስልጠናና የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች መመዝገቢያ ሶፍትዌር የማበልጸግ ሥራ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
የመጀመሪያውን ዙር የዲሞቢላይዜሽን ሥራ ለመጀመር የማዕከላት ርክክብ፥ የጥገናና የሎጅስቲክስ ግዥና አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለማማላት እየሰራን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት ለኮሚሽኑ ፕሮግራሞች መሳካት በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነር ተመስገን የአውሮፓ ህብረት ለመጀመሪያው ዙር ስራ ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነው አሁንም የህብረቱ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ሶፌ በበኩላቸው የኮሚሽኑ ሥራ ለሰላምና ለልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ የአውሮፓ ህብረት ለስራው መሳካት ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ለDDR ስራ ድጋፍ የ16 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።