በትግራይ ክልል “በDDR አተገባበርየማህበረሰቡሚና” በሚልርዕሰጉዳይላይ የማህበረሰብ ምክክር ተካሄደ፤
(መቐለ ታህሳስ 7 ቀን 2017ዓ.ም ብ/ተ/ኮ) ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል በጀመረው የDDR ፕሮግራም አተገባበር ሂደት የሕብረተሰቡ ሚና ምን መሆን አለበት? በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተወካዮች ጋር በመቀለ ከተማ ምክክር ተካሄደ፡፡
በምክክሩ ወቅት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የትግራይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ኮሌኔል ኪሮስ ወልደስላሴ እንደገለፁት የቀድሞ ተዋጊ ሴቶች፣ የወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረትና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በDDR እየተሳተፉ እንደሆነ ገልፀዋል። በፕሮግራሙ ተሳትፈው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የሚሰጣቸውን የመልሶ መቀላቀል ክፍያ በአግባቡ ስራ ላይ ሊያውሉ እንደሚገባ ኮሎኔል ኪሮስ ተናግረዋል። በየአከባቢው ማህበረሰቡ ለእነዚህ ተመላሾች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር የአርበኞች ኮሚሽን ኮሚሽር አቶ ናስር መምሁር በበኩላቸው ክልሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የአርበኞች ኮሚሽን አቋቁሞ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነ ጠቅሰው ወጣቶች በሚፈጠርላቸው መልካም አጋጣሚና በተሰጣቸው የመልሶ መቀላቀል ገንዘብ የተለያዩ ሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የብሐራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከUNICEF ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የDDR አተገባበርና የማህበረሰቡ ሚና፣ የወጣችና ሴቶች ተሳትፎ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች ምን መሆን እንዳለባቸው ምክክር ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተውጣጡ አመራሮች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የሀገር ሽግሌዎች፣ የትግራይ ክልል የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀት፣ የቀድሞ ተዋጊ የነበሩና በDDR ፕሮግራም ተሳትፈው ወደ ሲቪል ሕይወት የገቡ ግለሰቦች ቤተሰቦችም ተሳትፈውበታል፡፡